Sebket

አለማመኔን እርዳው
በመ/ር ኃይለማርያም ላቀው

«እምነት፣ ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረዳ ነው» ዕብ. 11፣1፡፡ የሰው ልጅ ተስፈኛ ወይም ተስፋ ያለው ፍጡር ነው፡፡ አዳም ቢበድልም እንኳን ቸሩ አምላክ በኋላ ዘመን ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው ተስፋ ሰጥቶታል፡፡ አዳምም የመዳኑን ነገር በእምነት ተስፋ በማድረጉ በጊዜው አግኝቶታል፡፡ እምነት ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር የምንገልጥበት፣ እርሱን ደስ የምናሰኝበት የሕይወት መሠረት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እምነት እግዚአብሔርን ደስ የምናሰኝበት ጥበብ መሆኑን ሲያስረዳ «ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይ ቻልም» ብሏል፡፡ ዕብ. 11፣6፡፡

በዘመነ ብሉይ የነበሩ በእምነት ጥን ካሬአቸው የተመሰከረላቸው አበውና እመው በእግዚአብሔር በመታመናቸው በሚያቃጥል የእሳት ነበልባል ውስጥ በመጣል፣ ወደ አንበሳ ጉድጓድ በመወርወር፣ በሰይፍ በመተርተር እምነታቸውን ገልጠዋል፡፡ እግዚአብሔርም በቅዱሳን የእምነት ጥንካሬ የልበ ደንዳኖችን ልብ ማርኳል፡፡ «ንጉሡ ናቡከደነጾር ለጣዖት አንሰግድም ብለው እምነታቸውን የገለጡትን ሠለስቱ ደቂቅን ርዝማኔው አስራ ስድስት ክንድ ከሚደርስ የእሳት ነበልባል ውስጥ በሰንሰለት አስሮ ቢወርወራቸውም ከሰውነታቸው አንዳች ሳይቃጠል በመዳናቸው፤ «በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ የሲድራቅ፣ የሚሳቅና የአብ ደናጎ አምላክ ይባረክ» ዳን. 3፣25 ሲል የሠለስቱ ደቂቅን አምላክ አክብሯል፡፡

በዘመነ ሐዲስ በሰው ፍቅር ተስቦ ወደዚህ ዓለም የመጣው ቸሩ አምላክ ለአገልግሎት ከመረጣቸው ሰዎች አንዳንዶቹ ምንም ዓይነት መሠረታዊ የሃይማኖት ዕውቀት አልነበራቸውም፡፡ እግዚአብሔር እነዚህን አላዋቂዎችን የመረጠው በዘመኑ በዕውቀታቸው የሚታበዩ ሰዎችን ዕውቀት ከንቱ ለማድረግ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጌታችን የዓለምን ጥበብ ከንቱ ለማድረግ አላዋቂዎችን እንደመረጠ ሲያስረዳ፤ «እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር እግዚአብሔር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ፤ እግዚአብሔር የሆነውን ነገር እንዲያጠፋ የዓለምን ምናምንቴ ነገር የተናቀውንም ነገር ያልሆነውንም መረጠ፡፡» ብሏል፡፡ 1ኛቆሮ.1፣26-29፡፡

እግዚአብሔር ለእምነት አገልግሎት ሰዎችን ሲመርጥ ሞኞች ጠቢባን ይሆናሉ፤ አላዋቂዎች ሀብተ እውቀት ያገኛሉ፤ ደካማዎች ብርቱዎች ይሆናሉ፡፡ አላዋቂ የነበሩት ተከታዮቹ ጠቢባን፤ ደካማ የነበሩት ብርቱዎች እስከሚሆኑ ድረስ ለቀጣይ የእምነት ሕይ ወታቸው ብርታት እንዲሆናቸው የተለያዩ ጥያቄዎችን ለጌታችን ያቀርቡ ነበር፡፡

ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይከተሉ ከነበሩ ሰዎች ለጌታችን ካቀረቡት ጥያቄ አንዱ «አለማመኔን እርዳው» የሚል ነው፡፡ ጌታችን የቃሉን ትምህርት ሰምተው የእጁን ተአምራት አይተው የተከተሉትን በሕይወት ሰጪ ትምህርቱ በነፍስ የተመሙትን ተስፋ የቆረጡትን፣ ባዶነት የሚሰማቸውን መንፈሳዊ ዝለት የገጠማቸውን ሲፈውስ፤ በተአምራቱ ደግሞ በሕማመ ሥጋ የታመሙትን ፈውሷል፡፡ የጌታችንን ሕይወት ሰጪ ትምህርት ፈልገው የተከተሉ አብዛኛዎች በተከፈለ ልብ ነበር፡፡ መድኃኒታችን የተከፈለ ልብ ያላቸውን ማረጋጋት፣ ያዘኑትን ማጽናናት ግብሩ በመሆኑ ድክመታቸውን ሳይሸሸጉ የሚቀርቡትን ፈጣን ምላሽ ይሰጣል፡፡

የጌታችን ደቀ መዛሙርት ልጁን እንዲፈውሱለት የወሰደው ሰው፤ ከእርሱና ከደቀ መዛሙርቱ የእምነት ማነስ የተነሣ ፍቱን መፍትሔ ቢያጣም ከጌታችን ዘንድ መጥቶ የእምነቱ ጉድለት በጌታችን እንዲስተ ካክልለት የልጁን ሕማም ሁኔታ ከዘረዘረ በኋላ፤ «ቢቻልህ ግን እዘንልን እርዳን» ማር.9፣22 የሚል ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ «ቢቻልህ የሚለውን» የጥርጣሬ ቃል «ቢቻልህ ትላለህ፤ ለሚያምን ሰው ሁሉ ይቻላል፡፡» በሚል ቃል ሲያርመው የተቸገረው ሰው አለማመኑ በእርሱ እንዲጠገንለት «በታላቅ ድምፅ አምናለሁ፤ አለማመኔን እርዳው» ብሎታል፡፡ ይህ ሰው አምናለሁ አለማመኔን እርዳው በማለት በእምነት ሕይወት ውስጥ ያለበትን ችግር ሳይሸሸግ መናገሩን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡

ምክንያቱም እያመን የማናምን፣ ንስሐ እየገባን የማንፀፀት፣ እየቆረብን ለሥጋ ወደሙ ክብር የማንሰጥ፣ እየቀደስን ያልተቀደስን ብዙዎች ነን፡፡ እኛም እናምናለን ነገር ግን እምነታችን በአንተ ይታገዝ እርዳን ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ ብዙ ሰዎች ክርስቶስ መወለዱን፣ መጠመቁን፣ ከሙታን መነሣቱን (ትንሣኤውን መግለጡን) ያምናሉ፡፡ በዚህ ሕይወት ውስጥ ያላቸውን ድርሻ እና ተስፋ ግን ይጠራጠራሉ፡፡ በሌላ አነጋገር እያመንን በእምነት ሕይወት ውስጥ አንኖርም ለዚህ ማለዘቢያ ግን እምነታችን፣ አለማወቃችንና ድካማችን በጌታችን እንዲደገፍ መማጸን ነው፡፡

በማቴዎስ ወንጌል ቅዱሳን ሐዋርያት የታመመውን ልጅ ለመፈወስ አቅም ያጡበትን ምክንያት ለመረዳት፤ «እኛ ልናወጣው ያልቻልን ስለምንድነው?» ሲሉ ጌታችንን ጠይቀውታል /ማቴ.17፣19/፡፡ ይህ ጥያቄ የእኛም ጥያቄ ነው፡፡ እኔ የተሰጠኝን ሓላፊነት ያልተወጣሁት ስለምንድነው? ያልቆረብኩት ስለምንድነው? ከልቤ ውስጥ የሚጉላላውን ቂም ያላወጣሁት ስለምንድነው? የበደልኩትን ያልካስኩት ስለምንድነው? የሚፈታተነኝን የሰይጣን ፈተና ማለፍ ያልቻልኩት ስለምንድነው? መንፈሳዊ ሕይወቴ ማደግ ያልቻለው፣ ራሴን ማወቅ መረዳት ያልቻልኩት ስለምንድነው? ብለን እንድንጠይቅ የቅዱሳን ሐዋርያት ጥያቄ ይጋብዘናል፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት እግዚአብሔር ከጎናቸው እያለ የእምነት ጉድለት ስለታየባቸው ማድረግ የሚገባቸውን ለመፈጸም አልቻሉም፤ ነገር ግን ልባቸውን የፈነቀለውን አንገብጋቢ ጥያቄ መጠየቃቸው መልካም ነበር፡፡ ምክንያቱም በእምነት ሊያደርጉት የሚቻላቸውን ነገር ማድረግ የተሣናቸው ስለእምነታቸው ጉድለት መሆኑን ጌታችን አስረግጦ እንዲህ በማለት ነግሯቸዋል፡፡ «እውነት እላችኋለሁ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ ይህን ሾላ ተነቅለህ በሌላ ቦታ ተተከል ብትሉት ይታዘዝላች ኋል» ሉቃ.17፣6 ብሏቸዋል፡፡ «ማመን፣ ያመኑትን ማድረግ» ከባድ ነገር ነው፡፡ ዛሬ ስለእምነት፣  በእምነት ሕይወት ስለመኖር፣ የእግዚአብሔርን ቃል መሠረት በማድረግ የቅዱሳንን ገድልና ትሩፋት በመግለጥ ብዙ ነገር ተነግሮናል፡፡ ነገር ግን በአብዛኛዎቻችን ቃሉ በጭንጫ ላይ የተዘራ ዘር ሆኖብናል፤ /ማቴ. 13፣20/ «ጌታችን በጭንጫ ላይ ዘር ወደቀ፤ ጥልቅ መሬትም ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ደረቀ» ያለውን ሲፈታ «በጭንጫ ላይ የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበል ነው፡፡ ነገር ግን ለጊዜው ነው እንጂ በእርሱ ሥር የለውም፤ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላል፡፡» ብሏል፡፡

በእምነት መንፈሳዊ ሕይወታቸው አልጸና ብሎአቸው ይቸገሩ የነበሩ ቅዱሳን አባቶቻችን ያቀረቡት ጥያቄ መሠረታዊ ምላሽ አግኝቶ፤ የሰውነ ታቸው ለልብሳቸው፤ የልብሳቸው ለጥላቸው አልፎ ሕሙም ከመፈወስ ሙት እስከ ማስነሣት ደርሰዋል፡፡ ይኸውም ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ በዚህም አገልግሎታቸው እንደ ሠመረላቸው መረዳት ይቻላል፡፡

እኛም «በሃይማኖት ስትኖሩ ራሳች ሁን መርምሩ» ተብሎ እንደተነገረን፤ በቅድሚያ መንፈሳዊ ሕይወቴ ያላደገው ለምንድ ነው? ብለን ያለንን የእምነት ጥንካሬና ድክመት መመዘን አለብን፡፡ በማስከተል እንደ ታመመው ልጅ አባት «አለማመኔን እርዳው» የሚል ጥያቄ አቅርበን፤ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል ፍጹም እምነት ሲኖረን ጌታችን እንዳለው ተራራ የሆነብን ትዕቢት፣ ከፊታችን የተደ ቀነው ክፋት፣ ምቀኝነት ከሕይወ ታችን ይነቀላል፡፡ እየወላወለ የሚያ ስቸግረን ልቡናችን ክት እንዲሆን ወይም እንዲሰበሰብልን «አለማመኔን እርዳው» ማለት አለብን፡፡ አለማመናችን በእግዚአብሔር ሲረዳ ባሕሩ እንደ የብስ ጸንቶልን እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ በባሕር ላይ እንረማመዳለን፡፡ በሌላ አነጋገር እግዚአብሔር አለማመናችንን ሲረዳው የሚሣነን ነገር የለም፡፡ «በእኔ የሚያምን ከእኔ የበለጠ ያደርጋል» ተብሎ ለቅዱሳን የተገባው ቃል የታመነ ነው፡፡ 

ያ በእምነት ያልጸናው ሰው ለእግዚአብሔር አምላኩ «አለማመ ኔን እርዳው» ሲል ያቀረበው ጥያቄ የሁላችንንም ሕይወት የሚወክል ነው፡፡ ዛሬ እምነቱ ሥርዓቱ፣ ትውፊቱ እያ ለን በፍጹም ልብ ያለማመን ችግር አለብን፡፡ ልጁ የታመመበት ሰው «አለማመኔን እርዳው ሲል» በአንተ ታምኜ የምኖርበትን ኃይል ለአንተ የሚገዛ ልብ እና ሕይወት ስጠኝ ማለቱ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ከአባቶቻችን የተቀበልነው እምነት የፈተና ጎርፍ ሳይሸረሽረው ነፋስ ሳያ ዘመው በዐለት ላይ ተመሥርቶ እን ዲጸናልን ዘወትር «ጌታ ሆይ አለማ መኔን እርዳው» ማለት አለብን፡፡ ያለማመናችን ችግር በእግዚአብሔር ካልተረዳ «ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ» በማለት ብቻ መንግሥተ ሰማያትን እንደማንወርስ ተነግሮናል፡፡ በመሆ ኑም ልባሞች ከመብራታቸው ጋር ዘይት ይዘው ሙሽራውን እንደጠበቁ፤ ባለማመን የጠወለገውን ሕይወታ ችንን በቃሉ ዝናምነት በማለምለም አለማመናችን በእግዚአብሔር ቃል መረዳት አለበት፡፡

ማንኛውም የሕይወት ውጣ ውረድ ቢያጋጥመን በእምነት ከጸናን የማናልፈው ነገር የለም፡፡ የማንዘለው የችግር እና የመከራ ግንብ፣ የማንሻገረው ባሕር እና መሰናክል የለም፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በእምነት ከእግዚአብሔር ጋር ከኖርን የሚያስፈራን አንዳች ነገር አለመኖሩን ሲያስረዳ «በሞት ጥላ መካከል እንኳን ብሔድ፤ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኩዝህ እነርሱ ያጽናኑኛል» መዝ. 22፣4 ብሏል፡፡

ነቢዩ እንደ ነገረን አፋችንን ሞልተን «በሞት ጥላ መካከል እንኳን ብሔድ ክፉን አልፈራም» በማለት በእምነት ማደግ አለብን፡፡ ቅዱስ ዳዊት በሕይወት ዘመኑ መውደቅ መነሣት ያጋጠመው ሰው ቢሆንም በእምነት በመጽናቱ ፍጻሜው ሠምሮ ልበ አምላክ ለመባል በቅቷል፡፡ በመሆኑም ዛሬ በመንፈሳዊ ሕይወታችን የተደቀነብንን ፈተና የምናልፈው በእምነት ነው፡፡ እግዚአብሔርን ደስ የምናሰኘው በእምነት ነው፡፡ የሚመጣውን ነገር በተስፋ የሚያስረዳንም እምነት በመ ሆኑ አለማመናችንን እርዳው እያልን መጮህ ይገባል፡፡

አለማመናችን በእግዚአብሔር ሲረዳ ወይም በእምነት ስንጸና ረድኤተ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ኃያላን የሆኑትን አራዊት ሳይቀር ገራም ያደርግልናል፡፡ በዘመነ ብሉይ ነቢዩ ዳንኤል ከአናብስት ጉድጓድ ሲወረወር የተራቡት አንበሶች ለነቢዩ ገራም የሆኑት የእምነት ሰው በመሆኑ ነው፡፡ በቅድስናቸው የተመሰከረላቸው ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አናምርት /ነብሮች/ እና አናብስት /አንበሶች/ የእግራቸውን ትቢያ እየላሱ የታዘዙላቸው በሥጋዊ ጥበብ ሳይሆን በእምነት ነው፡፡ ዛሬ ዲያብሎስ «እንደተራበ አንበሳ በፊታችን በሚያደባበት ዘመን የእምነትን ጥሩር መልበስ ያስፈልጋል፡፡ ለቀደሙት አባቶች ሥጋት የነበሩት ነገሮች ቀሊልና ታዛዥ እንደሆኑ ለእኛም ይሆኑልናል፡፡ ብዙ ጊዜ ፈቃደ ሥጋችን ፈቃደ ነፍሳችንን ሲጫነው የምንወደውን ሳይሆን የማንወደውን እናደርጋለን፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም» ሮሜ. 7፣19፡፡ ሲል እንደተናገረው፤ የሥጋችን ፈቃድ ብዙ ጊዜ «ነፍሴ ብይ፣ ጠጪ ደስ ይበልሽ» ወደ ማለት ቢያዘነብልም ቅሉ ወደ ፈቃደ ነፍስም መለስ ብሎ እኔ ማነኝ? ጉዞዬስ ወዴት ነው? ተስፋዬስ ማን ነው? ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት ፈቃደ ሥጋው እያየለ ሲያስቸግረው፤ በእንባው መኝታውን እያራሰ በእግዚአብሔር ፊት ቢያለቅስ፤ የኃጢአት አሽክላ እየተ ቆረጠለት በእምነቱ የሚደሰት ሰው ሆኗል፡፡

በእምነት ጉድለት በዲያብሎስ ሽንገላ የእምነት አቅም አጥተን ከቤተ ክርስቲያን ከቅድስና ሕይወት የራቅን ወገኖች፤ አለማመናችንን እግዚአብሔር እንዲረዳው ሳንሰለች ጥያቄ ማቅረብ አለብን፡፡ አስቀድመን እንደገለጽነው በእምነት ጉድለት ምክንያት ያጣነውን በረከት፣ ያጣነውን ጽናት እናገኛለን፡፡ ልባሞቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ይህን ለመፈጸም ለምን እኛን ተሳነን? ብለው እንደጠየቁ፤ እኛም ራሳችንን መጠየቅ አለብን፡፡ በጎ መሥራት ለምን ተሳነን?

የሰው ልጅ ወደ እምነት ፍጹም ነት ውስጥ ሲገባ ሁሉ ነገር በእግዚአብሔር እጅ እንደሆነ ይረዳል፤ ከጭንቀትም ያርፋል፡፡

በአቅማችንና በፈቃዳችን የተቸገረን መርዳት፣ አምላክን ከልብ መውደድ፣ ማመስገን የእምነት ሰው መገለጫ ናቸው፡፡

በእምነት የጸኑ አባቶችን በአንበሳ ጉድጓድ፣ በእሳት ውስጥ፣ በወህኒ ቤት በተጣሉ ጊዜ የተረዳና የእምነታቸውን ዋጋ የከፈለ እግዚአብሔር ዛሬም አለ፡፡ በመሆኑም መንፈሳዊ ሕይወታችንን በእምነት አሳድገን ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ያብቃን፡፡
  
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
 
 
ሀብዎሙ ዘይቤልዑ የሚበሉትን ስጡአቸው(ክፍል አንድ)
በመ/ር አፈወርቅ ወ/አረጋዊ
ማቴ. 14.16

ከዓለም አስቀደሞ የነበረ በማእከለ ዘመን ያለ ዓለምን አሳልፎ ለዘለዓለም የሚኖር፣ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው ቃል ነው፡፡ የሰውን ልጅ ለማዳን ከወደቀበት ለማንሣት ወደቀደመ ክብሩም ለመመለስ ከንጽሕተ ንጹሐን ከቅድስተ ቅዱሳን እመቤታችን ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ አምላክ ሰው ሆነ፡፡

በመዋዕለ ትምህርቱም የእጁን ተአምራት አይተው የቃሉን ትምህርት ሰምተው ከአሥር አህጉር ከብዙ መንደር ተውጣጥተው የአምስት ገበያ ያህል ሰዎች ይከተሉት ነበር፡፡

ከተከታዮቹም ውስጥ አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት፣ ሰባ ሁለቱ አርድእት፣ ሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት በጥቅሉ መቶ ሃያ ቤተሰብ በመ ሆን /የሐዋ.1.15/፤ በዋለበት እየዋሉ በአደረበት እያደሩ ትምህርት ከተአምራት ሳይከፈልባቸው ሥጋዊ ፍላጎታቸውን አሸንፈው ተከትለውታል፡፡

«እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን» /ማቴ 19.27/፤ በማለት የአገልግሎት ዋጋ ከጠየቁት ሐዋርያት በተጨማሪም ሌላ  ብዙ ሕዝብ ይከተለው እንደነበር ወንጌላዊው ማቴዎስ እንዲህ በማለት ጽፎልናል «ከገሊላም ከአሥር ከተማም ከኢየሩሳሌምም ከአይሁድም ከዮርዳኖስም ማዶ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት» /ማቴ. 4.25/፡፡

በዘመነ ብሉይ በነቢያት አድሮ ለሕዝቡ መልእክቱን ያስተላለፈ አምላክ ከነቢያት አንዱ በሆነው ልበ አምላክ ዳዊት ላይ አድሮ እንዲህ የሚል ቃል አናግሮ ነበር፡፡ «ወደ እርሱ ቅረቡ ያበራላችሁማል ፊታችሁም አያፍርም ይህ ችግረኛ ጮኸ እግዚብሔርም ሰማው ከመከራውም አዳነው» /መዝ. 33.5/፡፡

በምድራችን ላይ ብዙ ዓይነት ችግሮች ቢኖሩም ከረሀብ የበለጠ ችግር የለምና የራበው ሁሉ የሚበላውንና የሚጠጣውን ለማግኘት ወደ አምላኩ ይጮሃል፡፡ በሊቀ ነቢያት ሙሴ መሪነት ከግብፅ ባርነት ወደምድረ ርስት ሲጓዙ የነበሩ እስራኤላውያን በኃይለኛ ረሀብ ተመትተው ስለነበረ የምንበላውን ስጠን ብለው ወደ ሙሴ ጮኹ ይላል /ዘኁ. 21.4ጠ5/፡፡

ለቸርነቱ ወሰን ድንበር የሌለው፣ መግቦቱ የማይቋረጥ እግዚአብሔር ለተራቡት ሕዝብ መና ከደመና አዘነበላቸው፣ ውኃ ከዐለት ላይ አፈለቀላቸው፣ እነርሱም በሉ ጠገቡ ጠጡ ረኩ ይላል /ዘጸ. 16.8/፡፡

የፍጥረታት ሁሉ መጋቢ እግዚአብሔር አምላክ መሆኑን የተረዳው መዝሙረኛው፤ «የሁሉ ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል አንተም ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸዋለህ አንተ እጅህን ትከፍታለህ ሕይወት ላለው ሁሉ መልካምን /የሚጠቅመውን/ ታጠግባለህ» ይላል /መዝ.144.15/፡፡

ስለ እርሱ የተነገረው ትንቢተ ነቢያት ተፈጽሞ ሰው ሆኖ በመጣ ጊዜም በነቢያት ያስተላለፈውን ጥሪ አማናዊ በማድረግ፤ «እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደኔ ኑ ... ለነፍሳሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜ ቀሊል ነው» /ማቴ.11.28ጠ30/፤ በማለት የርኅራኄ ድምፁን አስምቷል፡፡

በዚህ ጥሪ መሠረት ልዩ ልዩ ችግር ያለባቸውን ማለትም በረሀብ የተጎዱትን ኅብስት አበርክቶ መግቧቸዋል፡፡ አካላቸው በበሽታ የደከመውን ፈውሶአቸዋል፡፡

ጌታችን የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አንገት መቆረጡንና በድኑን ወስደው መቅበራቸውን ከደቀ መዛሙርቱ በሰማ ጊዜ ብቻውን ወደምድረ በዳ ፈቀቅ አለ፡፡ «ሕዝቡም ሰምተው ከከተማዎቹ በእግር ተከተሉት እርሱም ወጥቶ የተከተሉትን ሕዝብ አየና አዘነላቸው ድውዮቻቸውንም ፈወሰ፡፡» በልዩ ልዩ ችግር ተጠምደው መከራ በርትቶባቸው፣ ደዌ ሥጋ ደዌ ነፍስ አሠቃይቶአቸው የመጡትን በሽተኞች ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ ፈወሳቸው፡፡ የሥጋ ረሀብተኞችንም ምግበ ሥጋን ሰጣቸው፤ በረሀበ ነፍስ የተጎዱትንም በቃሉ ትምህርት ፈወሳቸው፡፡ የእያንዳንዱን የችግር ቋጠሮ ሁሉ በአምላካዊ ጥበቡና ቸርነቱ ፈታላቸው እርሱ ሁሉን አዋቂ ነውና፡፡

ዛሬም እኛ ወደ እርሱ ከቀረብን ጉድለታችን ይሞላልናል፣ ያለው ይበረክትልናል፣ የራቀው ይቀርብልናል፣ አሳባችንን ችግራችንን በፍጹም እምነት በእርሱ ላይ እንተወው፤ /መዝ. 54.22/፡፡ የእኛ ድርሻ እርሱን መከተል ለእርሱ መታዘዝ ይሁን፤ በራት ላይ ዳረጎት እንዲሉ ሁሉ ይጨመርልናል /ማቴ. 6.33፡፡

ሁሉን ትተው የተከተሉት ደቀ መዛሙርቱ የእርሱ አገልጋዮችና የቅርብ ባለሟሎች ናቸውና፤ ለመምህራቸው ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀረብ ብለው በምስጢር፤ ቦታው ምድረ በዳ ነው አሁን ሰዓቱ መሽቷል ጊዜው አልፏል ወደመንደሮች ሔደው ለራሳቸው ምግብ እንዲገዙ ሕዝቡን አሰናብት፤ አሉት፡፡ እርሱ ግን ልብ ያሰበውን ኩላሊት ያመላለሰውን የሚመረምር ከአሳብ አስቀድሞ የሚታሰበውን የሚያውቅ አምላክ፤ በረሀብ የጠወለገ የደከመ ሰውነታቸው በበሽታ የተጎዳ አካላቸው በምግበ ሥጋ መጠንከር ነበረበትና፡፡ ደቀ መዛሙርቱን «የሚበሉትን ስጡአቸው እንጂ በረሀብ በተጎዳ ሰውነታቸው ሊሄዱ አያስፈልግም አላቸው፡፡»

በሥጋ አለስልሶ በደም አርሶ በጅማት አስሮ በአጥንት አጠንክሮ የፈጠረውን ሰውነት ለደቂቃ እንኳን ሳይዘነጋ በዝናብ አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ የሚመግብ አባት ነው፡፡
ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱ የምድርን ፍሬ አንዲቷን ቅንጣት በመቶ፣ በሺሕ አብዝቶ የፈጠረውን ፍጥረት ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ ጀምሮ ሳያቋርጥ ከትንኝ እስከ ዝሆን ከሰው እስከ እንስሳ ያለውን እርሱ ባወቀ መመገብ የሚገባውን ሁሉ የሚመግብ አምላክ ነው፡፡

ስለሆነም የእርሱን ርኅራኄ የሐዋርያትን መብትና ግዴታ ለመግለጥ፤ የሚበሉትን ስጡአቸው አለ፡፡ እነርሱም የአምላካቸውን የመምህራቸውን ትእዛዝ በፍጹም ፍቅር በመቀበል መስጠትስ ይቻል ነበር ነገር ግን ያለው ጥቂት ነው፡፡ ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ በቀር የለም ለዚህ ሁሉ ሕዝብ አይበቃም ነው ያሉት፡፡

አስደናቂው ነገር ደቀ መዛሙርቱ የምግቡን ማነስ ተናገሩ እንጂ ይህ አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ እንኳን ለሌላው ለእኛም አይበቃም፡፡ እኛ ምን እንበላለን የሚል የስስት የስግብግብነት አስተሳሰብም ሆነ ንግግር አላደረባቸውም፡፡ ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ግን በሰው ሰውኛው አመለካከት አለመብቃቱን ገልጸዋል፡፡

ዓለም እጅግ ብዙ ነገር ይፈልጋል ብዙ ነገር ይሰበስባል ያከማቻል ነገር ግን ያንሰዋል፡፡ የሰበሰበው ይበተናል የሞላው ይጎልበታል፤ ይገርማል በእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠ ከሆነ ግን ጥቂቱ ይበቃል፤ /ሉቃ. 10.42/፡፡

እርሱም የያዛችሁትን ያለውን አምጡልኝ አላቸው፡፡ አመጡለት በእርሱም እጅ ላይ አበረከተው፡፡ እኛም እንደ ደቀ መዛሙርቱ ያለንን ይዘን ወደ እርሱ እንቅረብ ከእርሱ መደበቅ የለብንም፤ አሥራቱን በኩራቱን ቀዳምያቱን ስሙ ለሚጠራበት ቤተ ክርስቲያን እንስጥ፤ ወደ እርሱ ይዞ መቅረብ ማለት ይህ ነውና ለእኛ በቅቶ ለሌላው ይተርፋል፡፡

ያለምንም ቅሬታ ማጉረምረም ትእዛዙን ተቀብለው የያዙትን ወደ አምላካቸው አቀረቡት፡፡ ምእመናን ቅር ሳይላቸው ሳያጉረመርሙ እንደ ደቀመዛሙርቱ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መቀበል አለባቸው፡፡ ጌታችንም የቀረበውን እንጀራ ባረከው፡፡ ከባረከው በኋላ ቆረሰው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው ሥራው ሁሉ ድንቅ ነውና የሰጣቸው ሁሉ በእጃቸው ላይ ይበረከት ነበር፡፡ «እግዚአብሔርን ሥራህ ግሩም ነው በሉት» /መዝ. 25.3/፡፡

ለጌታ የሰጡትን ከጌታም የተቀበሉትን እንጀራ በአካባቢው ለነበረው ሕዝብ ሁሉ ሰጡ አቀረቡ፤ ሕዝቡን አስተናገዱ፡፡ እነርሱም የመመገብ የማስተናገድ ሓላፊነት አገኙ፤ ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ከነበሩት ሁሉ ያልበላ አልተገኘም፡፡ መብላት ብቻ ሳይሆን እስከሚበቃቸው ድረስ በሉ አተረፉ፡፡ እውነት ነው ከአምላክ የተሰጠ ሁሉ ያጠግባል፡፡ ይትረፈረፋል፡፡

ቀድሞ በሊቀ ነቢያት ሙሴና በሊቀ ካህናት አሮን ላይ አድሮ፤ መና ከደመና አውርዶ፣ ውኃ ከዐለት አፍልቆ፣ አእላፈ እስራኤልን የመገበ ያጠጣ፣ ከሁሉ በላይ የሆነ፣ በሁሉ ያለ በሁሉ የሚሠራ ኃያል አምላክ፤ በብሉይ ኪዳን ሰው ሊደርስበት በማይችል ረቂቅ ጥበቡ ይሠራው የነበረውን መግቦት ሰው በመሆን በሚታይ በሚዳሰስ በሚጨበጥ ሰውነት /አካል/ እጁን ወደሰማይ በመዘርጋት፤ ሥርዓተ ጸሎትን አድርሶ፣ ሥርዓተ ምግብን አስተምሮ፣ እንጀራውን ፈትቶ /ቆርሶ/ እንካችሁ ብሎ በመስጠት ሰዎችን መገበ፡፡ እርሱ ከመገበ የማይመገብ ማን አለ) እሱ ከሰጠ የማይቀበልስ ማን አለ) ሁሉም ከተመገቡ በኋላ የተረፈው ማዕድ ሲነሣ አሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ ሆነ በእሱ ሥራ ጉድለት የለምና ከሴቶች ከልጆች በቀር አምስት ሺሕ ወንዶች ያህሉ ነበር፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት የተናገረው ቃል ምንኛ ያማረና የተወደደ እውነተኛ ቃል ነው፡፡ «በሉ እጅግ ጠገቡ ለምኞታቸውም ሰጣቸው ከወደዱትም አላሳጣቸውም» /መዝ.77.29/ እንዲል፡፡

እውነት ነው አምላካችን ሲመግበን እንጠግባለን፤ መልካም ምኞታችን የተሳካ ሥራችን የተከናወነ፣ ምርታችን የተትረፈረፈ፣ አገልግሎታችን የተቀደሰ፣ ዕውቀታችን የመጠቀ፣ አስተሳሰባችን የረቀቀ ከመሆን ባሻገር ከእኛ አልፎ ተርፎ ለሌላው የሚሆን የበረከት እንጀራ ይገኛል፡፡ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ በሥርዓቱ ስንመራና በተሰጠን የሕይወት መንገድ ወደቀኝ ወደ ግራ ሳንል መራመድ ስንችል ነው /ኢያ. 1.7/፡፡
ይቆየን፡፡
ሀብዎሙ ዘይበልዑ/ክፍል ሁለት/  የሚበሉትን ስጡአቸው /ማቴ. 14፣16 /

  በመ/ር አፈወርቅ ወ/አረጋዊ

ባለፈው ትምህርታችን «የሚበሉትን ስጡአቸው» በሚል ርእስ ቅዱሳን ሐዋርያት ለጌታችን ያቀረቡትን ጥያቄ፣ ጌታችን የመለሰላቸውን ድንቅ ነገር የሕብስቱ መባረክና መበርከትን በተመለከተ ማስነበባችን ይታወሳል፡፡ በዚህ እትም ደግሞ ካለፈው የቀጠለውን አቅርበናልና መልካም የሕይወትና የድኅነት ትምህርት ያድርግልን፡፡

በሊቀ ነቢያት ሙሴ መሪነት ወደ ምድረ ርስት ይጓዙ ለነበሩት ሕዝበ እስራኤል እግዚአብሔር እንዲህ አላቸው፡፡ «በሥርዓቴ ብትሔዱ ትእዛዛቴንም ብትጠብቁ ብታደርጉትም ዝናባችሁን በወቅቱ አዘንባለሁ፤ ምድሪቱም እህሏን ትሰጣለች፤ የሜዳውም ዛፎች ፍሬያቸውን ይሰጣሉ፤ የእህሉም ማበራየት በእናንተ ዘንድ እስከ ወይኑ መቆረጥ ይደርሳል፤ የወይኑ መቆረጥም እስከ እህሉ መዝራት ይደርሳል፤ እስክትጠግቡም ድረስ እንጀራን ትበላላችሁ. . .» ዘሌዋ. 26፣3-13፣ ዘዳ. 11፣13-17፡፡

በዚህ ርእሰ ትምህርት ላይ በትኩረት የምንመለከታቸው ዐበይት ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ሀ/ የእግዚአብሔርን ርኅራኄ፣ ቸርነትና መግቦት
ለ/ በመታዘዝ የሚገኘውን ታላቅ በረከት
ሐ/ ለጋስነትን
መ/ የችግር ተካፋይ መሆንን
ሠ/ ያለውን ማካፈልን
ረ/ የሥራ ድርሻን ማወቅ

በአጭሩ ለመረዳት ያህል እነዚህን አጉልተን ጠቀስን እንጂ፤ በዚህ ዐረፍተ ነገር ውስጥ እጅግ በርካታ ምስጢራት፣ ትምህርቶችና ትርጓሜዎች አሉ፡፡ ያቀረብናቸውን ነጥቦች በዝርዝር እንመልከት፡፡

መታዘዝ

የተራበውን ሕዝብ እንዲመግቡ ከጌታ የታዘዙት ደቀ መዛሙርቱ /ሐዋርያት/ ዓለምን በምግበ ሥጋ በምግበ ነፍስ እንዲጎበኙት ታዘዋል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም እንዲጠብቁት እንዲከባከቡት ቢታመም በተሰጣቸው ሥልጣን እንዲፈውሱት ሙሉ ሥልጣን ተሰጥቶአቸዋል፡፡ መታዘዝንም አስተምሮአቸዋል፡፡

ዓለም ይህን አውቆ ወደ መጋቢዎቹ ወደ ጠባቂዎቹ ቀርቦ ምግበ ሥጋውን ምግበ ነፍሱን ሊመገብ ይገባዋል፡፡ ከሚደርስበት መከራም ሊጠበቅና ሊፈወስ ይችል ዘንድ ወደ ጠባቂዎቹ ካህናት /ሐዋርያት/ በመቅረብ ጠባቂዎቹን አውቆ ከሌላው ሊሸሽ ግድ ነው፡፡ ይህ ሥርዓት ከመታዘዝ አንዱ ነውና፡፡

አበው ነቢያትና ሐዋርያት ለእውነት በመታዘዛቸው ጥቂቱን በማበርከት፣ መራራውን በማጣፈጥ፣ አስገራሚ ተአምራት በማድረግ፣ በጸሎታቸው የሕዝቡን ችግር አስወግደዋል፡፡
1. ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስ ለስራፕታዋ መበለት ትንሿን ዱቄት በማበርከት
2. ነቢየ እግዚአብሔር ኤልሳዕ ልጆቿ በዕዳ የተያዙባትን ሴት ጥቂቱን ዘይት በማብዛት፣ መካን ለነበረችው የሱነማይቱ ሴት ልጅ በመስጠት የአባትነት ድርሻቸውን ተወጥተዋል፡፡

ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው ነቢያቱም ሆነ ሐዋርያቱ በመጀመሪያ ታዛዦች ሆነው በመገኘታቸው ነው፡፡

የሚታዘዝ ይባረካል የማይታዘዝ ደግሞ ይረገማል፡፡ ሰው ለእግዚአብሔር ቢታዘዝ በረከትን ይቀበላል መርገሙ ከእርሱ ይርቃል፡፡

«እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እንቢ ብትሉ ግን ብታምፁ ሰይፍ ይበላችኋል፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሯልና» ኢሳ. 1፣19፣ ዘዳ. 11፣27፡፡

ምግባራትን ሁሉ መታዘዝ ይቀድማቸዋል በክርስትናው ዓለም መታዘዝ ማለት፤

- ለእግዚአብሔርና ለሕጉ
- ለወላጅና ለቤተሰብ
- ለአካባቢና ለጎረቤት
- እግዚአብሔር ለሾማቸው ካህናት
- በዕድሜ ለገፉ አባቶችና እናቶች

እንደ አስፈላጊነቱ መታዘዝ ይገባል፡፡ ሐዋርያት በቅንነት በመታዘዛቸው በሥራቸው ፍሬ አፍርተዋል፡፡ የሐዋ. 10፣33፡፡

ደቀ መዛሙርቱ ጌታችን ተከተሉኝ ሲላቸው ተከተሉት፡፡ ለሕዝቡ የሚበሉትን ስጡአቸው ሲላቸው ያላቸውን ያለንፍገት በማቅረብ  ሰጡ፡፡

እግዚአብሔር የመጣውን ትእዛዝ ሳንጠራጠር ሳንሟገት ጠቃሚ መሆኑን አውቀን በጽኑ እምነት ልንቀበል ያስፈልጋል፡፡

ሰማዕታት በእሳት፣ በስለት፣ በሰንሰለት በጅራፍ፣ በመገረፍ፣ በመስቀል በመሰቀል ይህንና ይህን በመሳሰለው መከራ ተፈትነው በሃይማኖታቸው ጸንተው ፈተናውን ድል አድርገው የተቀበሉትን ቃል ኪዳን ሳይጠራጠሩ መቀበል መታዘዝ ነው፡፡

ለጋስነት

ለጋስ ማለት ያልቅብኛል ይጎልብኛል ሳይል ሳይሳሳ በንፍገት ሳይሆን በቸርነት የሚሰጥ፤ ዘመድ ወገን ሳይል የሰው ወገን የሆነውን ሁሉ የሚረዳ፤ ለተራበው የሚያበላ፣ ለተጠማው የሚያጠጣ፣ ለተራቆተው የሚያለብስ ደግ ቸር የሆነ ሁሉ ለጋስ ይባላል፡፡

በዘመነ አበው በለጋስነት ከታወቁት አባቶች ታላቁን አብርሃምን ብንመለከት በየዕለቱ እንግዳ ይቀበል ነበር፡፡ በዚህ ግብሩም ታላቅ የበረከት አባት እንደሆነ ተነግሮለታል፡፡ ዘፍ. 12፣2፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም «የወንድማማቾች መዋደድ ይኑር እንግዶችን መቀበል አትርሱ በዚህ አንዳንዶች ሳያውቁ መላእክትን በእንግድነት ተቀብለዋል» ዕብ.13፣1-2 በማለት በቸርነት በለጋስነት የተገኘውን ረድኤት በረከት አሳይቷል፡፡

እግዚአብሔር በሀብት በዕውቀት በመግቦት የጎበኛቸው ሁሉ ለጋሶች፣ ሳይነፍጉ ሀብታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ዕውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ታማኝነታቸውን የሚሰጡ እንዲሆኑ ይህ ርእሰ ትምህርት ይናገራል፡፡ የሐዋርያት ለጋስነት ከብዙ ነገር ላይ ተነሥቶ ሳይሆን በትንሹ ላይ በመለገስ ለበረከት መብቃትን ያሳያል፡፡

ችግርን መጋራት

በዚች ምድር ላይ የተፈጠረ ፍጥረት ሁሉ በተለይም የሰው ልጅ ችግሩ ይለያይ እንጂ ችግር የማይደርስበት የለም፡፡

አንዱ የገንዘብ ችግር ባይኖርበት የጤና ችግር ይኖርበታል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ገንዘብና ጤንነት ተሟልተውለት በትዳር የሚቸገር፣ ትዳር ተሟልቶለት በልጅ እጦት የሚቸገር ሊኖር ይችላል፡፡ በዚህ በኩል የሚመጣውን ችግር መወጣት ያዳግተዋል፡፡ ጠቅለል ባለ መልኩ ስንመለከት ችግር ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ሁሉንም እንደየችግሩ ልንረዳና ልንረዳዳ፣ በችግሩ ልንጋራ፣ በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ወደ ሰርግ ቤት ከመሔድ ይልቅ ወደ ልቅሶ ቤት መሔድ ይሻላል ያለው፤ የተቸገሩትን መርዳት ያዘኑትን ማጽናናት ማረጋጋትን ሲያስረዳን ነው፡፡

የሐዋርያት ጥያቄ የጌታችንም መልስ በችግርና በችግረኞች ላይ የተደረገ ውይይትና መፍትሔም የታየበት ነበር፡፡ የመፍትሔው አካላት ለመሆን ፈቃደኞች እንሁን፡፡ 

ሐዋርያው «በአሁኑ ዘመን ባለጠጎች የሆኑትን መልካም እንዲያደርጉ በበጎ ሥራ ባለጠጎች እንዲሆኑ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው» 1ጢሞ. 6፣17-19 ይላል፡፡ መርዳት የሚችሉ አካላት በመርዳታቸው የችግር ተካፋዮች መሆናቸውን ማመን ያስፈልጋል፡፡

ድርሻን ማወቅ

ከትንሽ እስከ ትልቅ ከአገልጋይ እስከ ተገልጋይ ከመጋቢ እስከ ተመጋቢ ያለው የሥራ ድርሻውን ማወቅ በእጅጉ  ጠቃሚ ነው፡፡ የሥራን ድርሻ ሳያውቁ መንቀሳቀስ ፍምን በእጅ ጨብጦ አልቃጠልም እንደማለት ነው፡፡ ጆሮ የዓይንን እግር የእጅን ሥራ ሊሠራ እንደማይችል ሁሉ የሥራ ድርሻውን የማያውቅ እንዲሁ ነው፡፡

ዳታንና አቤሮን በሊቀ ነቢያት ሙሴና በሊቀ ካህናት አሮን የሥራ ድርሻ ውስጥ በመግባት ክህነታዊ ሥራ እንሠራለን ብለው አደጋ ላይ ወድቀዋል፤ በእሳት ተበልተዋል፤ ምድር ተከፍታ ውጣቸዋለች፡፡

ንጉሡ ግዝያንም በማን አለብኝነት ተነሣሥቶ በሥጋዊ ሥልጣኑ ተመክቶ ክህነታዊ ሥራ እሠራለሁ በማለቱ በለምጽ ተመትቶ ሞቷል፡፡

የሐዋርያት ድርሻ የሕዝቡን ችግር ወደ ፈጣሪያቸው ማቅረብ፣ የታዘዙትን በቅንነት መፈጸም፣ ያላቸውን ይዘው መቅረብ ነበር፡፡ የጌታችን ድርሻ ለሐዋርያት መመሪያ መስጠት፣ የቀረበውን ማበርከት፣ የተቸገረው ሕዝብ ከችግሩ እንዲላቀቅ ሐዋርያት ድርሻቸውን እንዲወጡ ማድረግ ነበር፡፡ ይህ ችግር ፈች አሠራር ለባለ ድርሻዎች ሁሉ አርአያነት አለው፡፡

በአጠቃላይ በየትኛውም የሥራና የአገልግሎት ድርሻ ሆነን ሕዝብን እንደምናገለግል በቅድሚያ ማወቅ ይኖርብናል፡፡ «የሚያስተምር ቢሆን በማስተማሩ ይትጋ፤ የሚመክርም ቢሆን በመምከሩ ይትጋ የሚሰጥ በልግስና ይስጥ፤ የሚገዛ በትጋት ይግዛ፤ የሚምር በደስታ ይማር» ሮሜ. 12፣7-8 ተብሎ ተጽፏል፡፡

«ሀብዎሙ ዘይበልዑ፤ የሚበሉትን ስጡአቸው» የተባሉ እነማን ናቸው? ለምን ተባሉ? መመሪያውንስ እንዴት ተወጡት? አሁን ከእኛ ምን ይጠበቃል? እንወያይበት፡፡

የሚመግብ ሆነ የሚመገብ ድርሻውን አውቆ ይሥራ፡፡ እንደተሰጠው ልዩ ልዩ ጸጋ መጋቢውም ተመጋቢውም ራሱን አሳልፎ ለፈጣሪው ይስጥ፡፡ መጋቢም ተመጋቢም የምግባቸው ዐውደ ማዕድ፤ ሲሳዮሙ ለቅዱሳን፤ የተባለ   እግዚአብሔር መሆኑን አምኖ መቀበል ብስለት ነው፡፡

የምንመገበውንና የሚመግቡንን ያዘዘልንና የሰጠን እግዚአብሔር ይመስገን አሜን፡፡